የ21ኛው የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኢትዮጵያ ባንኮችና ብርታት አሸናፊነት ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 18/1996/አዲስ ዘመን/ 21ኛው የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ትናንት በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄዱ የፍፃሜ ውድድሮች ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ ባንኮችና ብርታት ስፖርት ክለብ የበላይነታቸውን አሳይተዋል፡፡
በአንደኛ ዲቪዚዮን ኢትዮጵያ ባንኮች በ445 ነጥብ፣ በሁለተኛ ዲቪዚዮን ደግሞ ብርታት ስፖርት ክለብ በ181 ነጥብ አሸናፊ በመሆናቸው በአጠቃላይ ውጤት የዋንጫ ተሸላሚዎች ሆነዋል፡፡
ከአንድ ሺ 600 አትሌቶች በላይ በተካፈሉበት ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ባንኮቿ እመቤት ጥላሁን በርዝመት ዝላይ፣ በስሉስ ዘላይና 4Xበ100 ሜትር ዱላ ቅብብል ውድድሮች የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት የሻምፒዮናው ኮከብ አትሌት ሆና ተመርጣለች፡፡ እንዲሁም ከ2ኛ ዲቪዚዮን የቅዱስ ጊዮርጊሱ ሰለሞን ጽጌ በ10ሺና በ5ሺ ሜትር ያስመዘገበው የላቀ ውጤት ተተኪ አትሌትነቱን በተግባር ያስመሰከረበት ሆኗል፡፡
በአንደኛ ዲቪዚዮን የሴቶች ውድድር የኢትዮጵያ ባንኮች አትሌቶች 314 ነጥብ በማምጣት የበላይነታቸውን ሲያሳዩ፤ የቅርብ ተፎካካሪዎቻቸው የማረሚያ ቤቶች አትሌቶች በ193 ነጥብ 2ኛ ሆነዋል፡፡ በብራስልሱ የዓለም አገር አቋራጭ ሻፒዮና ላይ በስድስት ኪሎ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነችውን አትሌት መሰለች መልካሙን ያፈራው የመብራት ኃይል ቡድን በ61 ነጥብ የሦስተኝነትን ደረጃ ሲያገኝ፣ ኦሜድላ በ56፣ ኪቤ.አ.ድ በ13፣ እንጦጦ ተራራ በ4 ነጥብ ከአራተኛ እስከ ስድስተኛ ያሉትን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡
በአንደኛ ዲቪዚዮን ወንዶች መከላከያ በ260 የዋንጫ ተሸላሚ ሲሆን ፤ ማረሚያ ቤቶችና ኢትዮጵያ ባንኮች በ151ና በ131 ነጥብ 2ኛና 3ኛ ሆነዋል፡፡
ኦሜድላ በ77.5 ነጥብ 4ኛ ሲወጣ መብራት ኃይል፣ ተገን፣ ኦኒንስከነንና ብሩህ ተስፋ በ32፣ በ27 ፣ በ15ና በ8 ነጥብ ከ5ኛ እስከ 8ኛ ወጥተዋል፡፡
በሁለተኛ ዲቪዚዮን ወንዶች ትዕግስት ፍሬ በ115 ነጥብ ለዋንጫ ተሸላሚነት ሲበቃ፤ ላፍቶ አካባቢ በ107 ነጥብ 2ኛ፣ ነጋሽ ስፖርት ክለብ በ78 ነጥብ 3ኛ፣ ብርታት በ76 ነጥብ 4ኛ እንዲሁም አድማስ በ57 ነጥብ 5ኛ ሆነዋል፡፡
ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በ50 ነጥብ 6ኛ ሲወጣ ፍሬ ፀጋ በ44 ነጥብ 7ኛ፣ በሁለት ነጥብ የተበለጠው እንጦጦ ተራራ 8ኛ፣ ኪ.ቤ.አ.ድ. በ41 ነጥብ 9ኛ ሆነዋል፡፡ ሀኒና ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለቦች በ24ና 20 ነጥብ 10ኛና 11ኛ በመውጣት ውድድራቸውን አጠናቀዋል፡፡
በሁለተኛ ዲቪዚዮን ሴቶች ብርታት ስፖርት ክለብ በ105 ነጥብ ሻምፒዮናውን በድል ሲያጠናቅቅ ላፍቶ አካባቢ በ67 ነጥብ የሁለተኝነትን ደረጃ አግኝቷል፡፡ አድማስ፣ ነጋሽ ፣ ደሳለኝና ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ከ3ኛ እስከ 6ኛ ያሉትን ደረጃዎች ተቆጣጥረዋል፡፡ እንዲሁም ተገን፣ ሀኒ፣ ፍሬ ፀጋና ትዕግስት ፍሬ በ36፣ በ34፣ በ33ና በ10 ነጥቦች ከ7ኛ እስከ 10ኛ ያሉትን አራት ደረጃዎች ይዘዋል፡፡
በሻምፒዮናው በስፖርታዊ ጨዋነትና ሽብርቅ ጐልተው የወጡት ከአንደኛ ዲቪዚዮን መብራት ኃይል በ87 ነጥብ፣ ከሁለተኛ ዲቪዚዮን ላፍቶ አካባቢ በ76 ነጥብ የዋንጫ ተሸላሚዎች ሆነዋል፡፡
ትናንት በተካሄዳ የፍፃሜ ውድድሮች በአንደኛ ዲቪዚዮን 5ሺ ሜትር ሩጫ የኢትዮጵያ ባንኮቹ ሁሴን አድነው፣ የኦሜድላው ዳኜ ዓለሙና የኦሜድላው ሳህሌ ዋርጋው የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳሊዎችን አግኝተዋል፡፡
በተመሳሳይ 4X100 የሴቶች ዱላ ቅብብል የኢትዮጵያ ባንኮች፣ የመብራት ኃይልና የማረሚያ ቤቶች በወንዶች የኢትዮጵያ ባንኮች፣ የመከላከያና የመብራት ኃይል ተወዳዳሪዎች ከ1ኛ እስከ 3ኛ በመውጣት ክለባቸውን አስጠርተዋል፡፡
በወንዶች 4Xበ400 ሜትርም የኢትዮጵያ ባንኮች፣ የመከላከያና የመብራት ኃይል አትሌቶች የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ በማግኘት የበላይነታቸውን ሲያሳዩ በ800 ሜትር የኪ.ቤ.አዱ አብዮት አበበ፣ የብርታቱ ከበደ ጫላና የአሞዴአሱ ደረጃ ተሎሳ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ወጥተዋል፡፡
በሁለተኛ ዲቪዚዮን 400 ሜትር ሴቶች አበባ መገርሳ፣ ቆንጂት ዱባለና አንሰኔ ዳባ የመጀመሪያዎቹን ሦስት ደረጃዎች ሲያገኙ በወንዶች 3ሺ መሰናክል የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጆቹ ሀብቴ ዲባባና አብርሃም ገብረ መድህን የወርቅና የነሐስ ሜዳሊያ አግኝተዋል፡፡ የፍሬ ፀጋው አጫዋች ቢረዳ የብር ሜዳሊያ ወስዷል፡፡
በአንደኛ ዲቪዚዮን የ1ሺ 500 ሜትር የሩጫ ውድድር የማረሚያ ቤቱ ሳሙኤል ዳዴ ወርቅ ሲያገኝ ሰይፉ ነፍሴ ከኢትዮጵያ ባንኮች፣ አዱኛ አሰፋ ከማረሚያ ቤቶች ብርና ነሐስ አግኝተዋል፡፡
በሴቶች 5ሺ ሜትር እታለማሁ ኪዳኔ ከኦሜድላ 1ኛ፣ ስንታየሁ እጅጉና ብዙነሽ በቀለ ከኢትዮጵያ ባንኮች 2ኛና 3ኛ በመውጣት አሸናፊዎች ሆነዋል፡፡
በሴቶች ከፍታ ዝላይ የማረሚያ ቤቶቿ ሃይማኖት በቀለ 1ኛ፣ የኢትዮጵያ ባንኮቿ ሐረገ ወይን መንግሥቱ 2ኛ፣ በድጋሚ የማረሚያ ቤቶቿ መቅደስ በቀለ 3ኛ በመውጣት የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳሊያዎችን አጥልቀዋል፡፡ በተመሳሳይ የወንዶች ውድድር አንተነህ ታምሩ፣ ዴሮ ቶላና አበዲሳ ታደሰ ሦስቱም ከመከላከያ ከ1ኛ እስከ 3ኛ በመውጣት አንፀባራቂ ድል ተቀዳጅተዋል፡፡
በሻምፒዮናው ማጠናቀቂያ ላይ ናይጄሪያ አቡጃ በተካሄደው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ላይ ተካፍላ ከመጣች በኋላ ባጋጠማት ሕመም ምክንያት ሕየወቷ ላለፈው የኢትዮጵያ ባንኮቿ አትሌት ርብቃ ጭናሽ የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት ተደርጓል፡፡
አሸናፊ አትሌቶቸና ክለቦች የተዘጋጀላቸውን የዋንጫና የሜዳሊያ ሽልማት ከዕለቱ የክብር እንግዳ ከአዲስ አበባ ወጣቶችና የሜዳሊያ ሽልማት ከዕለቱ የክብር አንግዳ ከአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዘሪሁን ቢያድግልኝ፣ ከአዲስ አበባ አትሌቴክስ ፊዴሬሽን ፕሬዚዳንት መቶ አለቃ ደምሳሽ ኃይሉና ከሌሎች ተጋባዥ እንግዶች እጅ ተቀብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባልና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ መኮንን እንደገለጹት፣ የዘንድሮ ሻምፒዮና ካለፉት ሃያ ሻምፒዮናዎች የተሻለ ነው፡፡
ባለፉት ሻምፒዮናዎች የተካፋይ ክለቦች ቁጥር ከሃያ አይበልጥም ፤ ዘንድሮ 34 ክለቦች መካፈላቸው የሻምፒዮናው ተፈላጊነት እየጐላ መምጣቱን ያመለክታል ብለዋል፡፡
ለሻምፒዮናው ድምቀትና ውበት ከሰጡት ነገሮች መካከል የፌዴሬሽኑ የቴክኒክና የሥነ-ሥርዓት ኮሚቴ ለክለቦች ባስተላለፈው ጥብቅ መመሪያ መሠረት ክለቦቹ ለመመሪያው ተገዢ መሆናቸው እንደሆነ ጨምረው ገለጸዋል፡፡
የዘንድሮው ሻምፒዮና ለቀጣይ ሻምፒዮናዎች የሚረዳ ልምድ እንደተገኘበት የጠቆሙት አቶ ብርሃኑ፤ ውድድሩን ስፖንሰር ላደረጉት ለብሔራዊ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤትና ለሞሃ ለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪ ምስጋናቸውን አቅረበዋል፡፡